የባለ ሽቶዋ ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት አስደናቂ ታሪክ / ከገድላት አንደበት | ethiopian orthodox | EOTC tv | የቅዱሳን ታሪክ

ቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት፡- ስለ ማርያም እንተ እፍረት (ባለ ሽቱዋ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ላይ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› በማለት ተናግሮላታል፡፡ ማቴ 26፡13፡፡
የማርያም እንተ እፍረትን ገድሏንና ድርሳኗን የጻፈላት ታላቁ የቤተክርስቲያናችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ገድሏ ላይ ስለ እርሷ የተጻፈውን ቀጥለን እንይ፡- ማርያም እንተ ዕፍረት ሁልጊዜ ከነጭ ሐር የተሠራ ልብስ የምትለብስ፣ ከሽቱ ሁሉ ይልቅ የሚበልጥ ውድ ሽቱን ትቀባ ነበር፡፡ በወርቅም ታጌጥና በክፉ ሥራ ሁሉ ጸንታ የምትኖር ሴት ነበረች፡፡ ጠላት ዲያብሎስም የዚህን
ዓለም ጣዕም አጣፈጠላት፡፡ ነገር ግን ስለዚህች ሴትና ስለ ኃጥአን ሁሉ ጌታችን ከጌትነቱ ከፍታ ሳይለወጥ
ከልዑል ዙፋኑ ወረደ፡፡ በሰዎች መካከልም ከእነርሱ እንደ አንዱ እየተመላለሰ አስተማረ፡፡
አንድ ቀን እንደልማዷ ማርያም እንተ ዕፍረት ነጭ ሐር ለብሳ፣ አጊጣና ተኳኩላ ፊቷን በመስታወት አይታ ውድ ሽቱ ተቀባች፡፡ ጉንጮቿ ቀያዮች፣ ዓይኖቿ የተዋቡ ሆነው ደም ግባቷ በጣም አማራት፡፡ እንደዚህ እየተመለከተች አንድ ሰዓት ያህል ቆየች፡፡ ከዚህ በኋላ መልካም አሳብ በእርሷ ላይ አድሮ እንዲህ አለች፡- ‹‹ይህን ሁሉ ታስወግድ ዘንድ መልኬንም ትለውጥ ዘንድ ሞት ትመጣ የለምን? ይህ መልካም ሽታ ወደ ትልነትና ወደ መሽተት ይለወጣል፡፡ ይህስ ብርታት ፍጻሜው ጉስቁልናና ድካም አይለምን? ሊቀርቡኝ የሚወዱትስ የሚርቁኝ አይደሉምን? እንደዚህስ ከሆነ ዘለዓለም ከጥፋትና ከኩነኔ በቀር
እንግዲህ ምን አገኛለሁ? የዚህን ዓለም ገንዘብ ብገዛ፣ ብነዳ ከድካም በዐይኖቼም ዕንባን ከማፍሰስ የሚያድነኝ ይኖራልን? ወይስ ይህ ሁሉ ከሞት ያድነኝ ዘንድ ይችላልን? ነፍሴ ሆይ! እንግዲህ ሁሉን ለሚገዛ ጌታ ምን ትመልሻለሽ? ከእውነተኛው ፈራጅ ዘንድ በአንቺ ላይ ትእዛዝ በመጣ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ! ንስሐ በሌለበት፣ ነፍስ የተናቀች በምትሆንበት ጩኸት፣ ልቅሶና ጩኸት ባለበት ቦታ የሚረዳሽ ማነው? ነጭ ሐርና ኅብሩ ልዩ ልዩ የሆነ ልብስ በመልበስ ደስ የምትሰኝ ሥጋዬ ሆይ
በክብር ባለቤት በእግዚአብሔርና በመላእክቱ ፊት ራቁትሽን በቆምሽ ጊዜ እንዴት ትሆኛለሽ? ነፍሴ ሆይ!
በዚህ ዓለም የተደሰትሽው ምን ይጠቅምሻል?…›› እያለች ራሷን መመርመር ጀመረች፡፡ መድኃኒት ታገኝ ዘንድም የአመለከታትን አታውቅም፡፡ ከዚህ በኋላ በማመን ጸንታ እንዲህ ብላ አሰበች፡- ‹‹ስለ
ኃጥአን ወደዚህ ዓለም የመጣ ስለ እነርሱ በመካከላቸው እንደሰው የተመላለሰ ይህ አይደለምን? የኃጢአተኛን መመለሱን ነው እንጂ ሞቱን አልሻም ያለስ እርሱ አይደለምን? ነፍሴ ሆይ ምሕረትስ ቅርብ ናት ባለመድኃኒትም የራቀ አይደለም ሌላ መድኃኒትሽን ተስፋ የምታደርጊበትስ አለን? መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዲቱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልጋት የሚሔድ አይደለምን? ባገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከማታል፣ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሷ ደስ የሚሰኝ አይደለምን? እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ የሚል እርሱ መድኃኒት ክርስቶስ ነው፡፡ እንደዚህ ከሆነ ለምን እሰንፋለሁ? ለምንስ ንስሓ አልሻም? እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ወደ እርሱ ሄጄ ራሴን በፊቱ እክዳለሁ›› ብላ ካሰበች በኋላ ተጽናናችና በፍጥነት ተነስታ ግንዘቧን፣ የገዛችውን ወርቋንና ብሯን ሁሉ ሰበሰበች፡፡ ‹‹ምን አደርጋለሁ ይህን ገንዘብ ወስጄ
ብሰጠው አይቀበልም እርሱ ፈጣሪ፣ ጌታና የዓለም መድኃኒት ነውና›› ብላ አሰበች፡፡ ከዚህ በኋላ ሽቱ
ወደሚሸጥ ሰው ፍለጋ ሄደች፣ ያን ሰው ከጥንት ጀምሮ ታውቀው ነበርና ከእርሱ ዘንድ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቱን ገዛችና በደስታ ስትሄድ እነሆ ሰይጣን በወርቅ ያጌጠች ሴት መስሎ ወደ እርሷ መጣ፡፡ የዚህን ዓለም ምኞት እያጣፈጠ ይነግራት ጀመር፡፡ መብላትን፣ መጠጣትን፣ ያማረ ልብስ መልበስን፣ ሽቱ መቀባትን… ይህን ሁሉ ያሳስባት ጀመር፡፡ ጌታችንም በይቅርታው ብዛት
የጠላት ዲያብሎስን ክፋት ገለጠላትና ‹‹ለበደልና ለኃጢአት ሥራ የተዘጋጀሁ አድርገኸኛልና ኃፍረትና
ጉስቁልናንም በእኔ አምጥሃልና አንተ ሰይጣን ከእኔ ወግድ›› ብላ በቁርጥ ነገር መለሰችለት፡፡ ጠላት
ዲያብሎስም የሃይማኖቷን ጽናት ባየ ጊዜ ከእርሷ ሽሽቶ ፈሪሳዊ ወደሚሆን ስምን ወደሚባል ሰው ዘንድ ሄዶ ልቡናውን ያውከው ጀመር፡፡ እርሱም ጌታን በቤቱ ማዕድ ይመገብ ዘንድ ጋብዞት ነበርና፡፡ በልቡናው ያደረው ክፉ ሰይጣንም እንዲህ ብሎ እንዲናገር አደረገው፡- ‹‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ኃጢአተኛ እንደነበረች አያውቅም
ነበር?›› ብሎ እንዲያስብ አድረገው፡፡ ማርያም እንተ ዕፍረት ለጌታችን ያቀረበችው ልመናዋና
ንስሓዋ ይህ ነው፡- ‹‹ማርያም እንተ ዕፍረትም ደጆቸ ተከፍተው አገኘች፣ ያለማፈር ገብታ በፍጹም እምነት
ከእግዚአብሔር ወልድ ዘንድ ቀረበችና በስተኋላው ቆማ ልመናን አቀረበች፣ እያለቀሰችም በእንባዋ ታርሰው
ጀመረች፣ በራስ ፀጉሯም ታብሰው እግሩንም ትስመውና ሽቱ ተቀባው ነበር፡፡ በልቅሶና በዕንባ ሆና እንዲህም እያለች ልመናን አቀረበች፡- ‹ነፍስንና ሥጋን የምታድን የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ሆይ! የሕይወት ምንጭ ሆይ! ሕይወቷን ወዳሳመርክላት ወደ አገልጋይህ ተመልከት፡፡ እኔ
ግን አንተን በድያለሁ፣ እንደ እንስሳ ሆንሁ፣ እንደ እነርሱም የተቆጠርሁ ሆንሁ፣ ኃጢአኛና በደለኛ የምሆን እኔን አቤቱ ይቅር በለኝ፣ ማረኝ፣ ከኃጢአት ቀንበር በታች ሆኜ ለሰይጣን ተገዝቻለሁና ጌታዬ ሆይ! ከሰይጣን እጅ አድነኝ፣ የንስሐ ቀንበርንም እሸከም ዘንድ የበቃሁ አድርገኝ፣ የምሕረትህንም በር ክፈትልኝ፣ ጌታዬ ሆይ! ይቅርታህንና ሥርየትህን ተስፋ አድርጌ ወደ አንተ የመጣሁ ባሪያህን ተቀበለኝ› እያለች ፍጹም በተሰበረ ልብ ሆና ልመናን አቀረበች፡፡ ዳግመኛም ‹ነፍሴ ሆይ መድኃኒትሽን እንዴት አትሽም? እነሆ መድኃኒት ክርስቶስ በዚህ አለና ለምንስ ትዘገያለሽ? እነሆ የሕይወት ውኃ ምንጭ መጥቶልሻልና ከቆሻሻነትሽስ ለምን ቶሎ አትነፂም? ለደዌሽስ ፈውስን አትፈልጊምን?› አለች፡፡ ዳግመኛም
‹ከንቱ ነገርን ስትመለከቱ የኖራችሁ ዐይኖቼ ሆይ! ጌታን ታዩ ዘንድ ተሰጣችሁ፤ ርኩስን የምትዳስሱ እጆቼ ሆይ! የሰማያዊ ጌታን እግር ትዳስሱ ዘንድ ሰጣችሁ፤ ኃጢአተኛ ነፍሴ ሆይ! እነሆ ፈጽሞ ከፍ ያለ ባለሟልነትን አገኘሽ፤ ስላደረገልኝ ምን እከፍለዋለሁ› እያለች ታላቅ ልቅሶን አለቀሰች፡፡ የጌታንም እግር ይዛ በእንባዋ እያራሰች በፀጉሯ ታብስ ጀመር፡፡ አስቀድማ በልቧ እንዲህ ብላ አስባለችና ‹በጌታ ፊት ባለሟልነትንስ ካገኘሁ ወደ እርሱ ዘንድ እንድቀርብ ያደርገኛል፡፡ በሥራዬም ክፋት ካበረረኝ
ግን ዳግመኛ አልድንም› ብላ አስባ ነበር፡፡ ከጌታም ባለሟልነትን ባገኘች ጊዜ ጨክና በራሱ ላይ ሽቱውን
ጨመረች፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋርም ልቅሶንና ልመናን አላቋረጠችም፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በእርሷ ላይ
እንደበዛ ባየ ጊዜ ጠላት ዲያብሎስ በእርሷ ላይ ታላቅ መቅናትን ቀናባት፡፡ ተቆጥቶም ወደ ስምዖን ተመልሶ ልቡን አወከው፡፡ ‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ኃጢአተኛ እንደሆነች ያውቅ ነበር› እንዲል አደረገው፡፡ ጌታችንም ስምዖንን ሁሉ ከእርሱ እንዳልተደበቀና ሀሳቡንም እንዳወቀበት እንዲረዳና እግዚአብሔርም በደለኞችን ማዳንና ከኃጢአታቸው ማንጻት እንደሚችል ያውቅ ዘንድ እንዲያስተውል አደረገው፡፡›› ማርያም እንተ ዕፍረት ወይም በሌላኛው ስሟ ማርያም እኅተ አልዓዛር ትባላለች፡፡ ጌታችንን በቤታቸው ተገኝቶ ሳለ እኅቷ ማርታ ለአገልግሎት ስትደክም ማርያም ግን ከእግሩ ሥር ተቀምጣ ቅዱስ ቃሉን በመስማቷ ጌታችን ‹‹ማርያምስ የማይቀሟትን መልካም ዕድል መረጠች›› በማለት መስክሮላታል፡፡ ሉቃ 10፡38-42፡፡ ቀድሞ በዝሙት የኖረችበትን አስከፊ ሕይወት በመተው በቆራጥ ኅሊና ፍጹም ንስሓ ገብታ ገንዘቧን ሁሉ አውጥታ እጅግ ውድ የሆነውን ሽቱ ገዝታ ጌታችንን ስትቀባው ጌታችንም
በፍጹም ንስሓዋ ተደስቶ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል›› በማለት አስደናቂ ትእዛዙን የሰጠላትና ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ወገን የደመራት ቅድስት ናት፡፡ ማቴ 26፡6፡፡
የቅድስት ማርያም እንተ ዕፍረት ረድኤት በረከቷ ይደርብን
#ethiopianorthodox #ገድል #ስንክሳር
#AncientEthiopiaጥንታዊቷኢትዮጵያ | Ancient Ethiopia - ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ | ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ | Ancient Ethiopia | ancientethiopia | AncientEthiopia - ጥንታዊቷኢትዮጵያ | ancient ethiopia - ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ | ኦርቶዶክስ ተዋህዶ | ethiopianorthodox
| የኢትዮጵያኦርቶዶክስ | የኢትዮጵያኦርቶዶክስተዋህዶ | የኢትዮጵያኦርቶዶክስተዋህዶቤተክርስቲያን

Пікірлер: 3

  • @aberashkassa3056
    @aberashkassa30562 ай бұрын

    ❤ቃለ ህይወት ያሰማልን

  • @fikrtegetahun5678
    @fikrtegetahun56782 ай бұрын

    Kalehewot yasemalen kenatachen bereket ykfelen.🙏

  • @abrehamsolomon2458
    @abrehamsolomon245811 ай бұрын

    ቃለ ህይወት ያሰማልን

Келесі