פרשת שמיני-ፓራሻት ሽምኒ

በእግዚአብሔር እርዳታ ቅዳሜ የሚነበበው ሳምንትዊ የኦሪት ክፍል ከኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ 9 ቁጥር 1 እስከ ምዕራፍ 11 ቁጥር 44 የሚነበብ ሲሆን፤ ፓራሻት ሽሚኒ በመባል ይታወቃል። ባለፈው ሳምንት ባነበብነው የኦሪት ክፍል መምህራችን ሙሴ እንዴት በሰባቱ ቀናት ካህናት በድንኳኑ የሚደረገውን ሥነ ሥርዓት መፈፀም እንዳለባቸው እንዳስተማራቸው አይተናል። ይህ ሳምንታዊ የኦሪት ክፍል ደግሞ የሚያተኩረው በድንኳኑ መመረቂያ ቀን ይሆናል። ይህ ቀንም የመጋቢት የመጀመሪያው ቀን (የጨረቃ በዓል) ሲሆን፤ ይህ ምረቃ የሚከናወነው ደግሞ በአሮን እና በልጆቹ አማካይነት በስምንተኛው ቀን ነው። መምህራችን ሙሴ ለአሮን እጣኑ እንዴት እንደሚቀርብ ካስተማረው በኋላ፤ እግዚአብሔር መንፈሱን በድንኳኑ ላይ እንዲያሰፍር ፀሎት ያቀርባሉ። እግዚአብሔርም ፀሎታቸውን ሰምቶ ወዲያውን ከድንኳኑ እንደወጡ መንፈሱን በድንኳኑ ላይ ያሰፍራል። በዚህ ሁኔታ ሥነ ሥርዓቱ እየተካሄደ እያለ፤ ናዳቭ እና አቪይሁ የተባሉት የአሮን ልጆች እጣኑን ለማቃጠል ወደ ድንኳኑ ይገባሉ።

Пікірлер

    Келесі