➕ የዘወትር ሰይፈ ሥላሴ ፀሎት🙏✞ እንኳን በሰላም በጤና አደረሳቹ አደረሰን!🙏➕ የዘወትር ሰይፈ ሥላሴ ፀሎት ያድምጡ፣ ይፀልዩ!

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ይባላልን?
እንኳን ለበዓለ ሥሉስ ቅዱስ በሰላም አደረሳችሁ!
እግዚአብሔር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በመፍጠር እና በመሳሰሉት አንድ ሲሆን በስም፣ በአካል፣ በግብር ደግሞ ሦስት ነው፡፡ ይህ መሠረታዊው የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ምሥጢር ነው፡፡ በዚህች ምንዱብ ጦማር ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ብዙ ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ነገር ግን በተለምዶ እና በተደጋጋሚ የምትፈጸም አንዲት ስህተት ስላለች እርሷን ለመጠቆም ብቻ ነው፡፡
እርሷም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሚለውን የተለምዶ አባባል የምትመለከት ናት፡፡ እግዚአብሔር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ አንድ ነው ስንል በጌትነትም አንድ ነው ማለታችን ነው፡፡ ጌትነት ለእግዚአብሔር የባሕርዪው ነው ማለታችን የገዛ ገንዘቡ እንጂ ከማንም ያልተቀበለው ማለታችን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አማልክት ዘበጸጋ እንዳሉ ሁሉ አጋእዝት ዘበጸጋም አሉ፡፡
ለአማልክት ዘበጸጋ ሊቀ ነቢያት ሙሴን መጥቀስ እንችላለን፡፡ "እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ" ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዘጸ ፯፥፩። ደግሞም "እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ" የሚለው ቃል ይኽንኑ ያመለክታል፡፡ መዝ ፹፩፥፮። አማልክት የተባሉ ቅዱሳን ናቸው፡፡
ለአጋእዝት ዘበጸጋም ደግሞ አበ ብዙሃን አብርሃም ጌታ እየተባለ መጠራቱን እንጠቅሳለን፡፡ ዘፍ ፲፰፥፲፪፣ ፳፬፥፵፪። እንዲሁም ደግሞ መስፍኑ ኢያሱ ሊቀ መላእክቱን ጌታዬ ብሎ ጠርቶታል፡፡ "እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁን መጥቼአለሁ አለ። ኢያሱም ወደ ምድር በግምባሩ ተደፍቶ ሰገደና። ጌታዬ ለባሪያው የሚነግረው ምንድር ነው? አለው።" ኢያ ፭፥፲፬።
የእግዚአብሔርን የባሕርዪ አምላክነት እና ጌትነት ከቅዱሳን የጸጋ አምላክነት እንድንለይ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ የነገሥታት ኝጉሥ እየተባለ ተጠርቷል፡፡ የአማልክት አምላክ ለሚለው አጠራር የሚከተሉትን የመጽሐፍ ክፍሎች ማየት ይቻላል፡፡
፩᎐ የአማልክት አምላክ
"እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ" ዘዳ ፲፥፲፮።
"የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር፥ የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር እርሱ አውቆታል" ኢያ ፳፪፥፳፪።
"የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፥ ከፀሓይም መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት።" መዝ ፵፱፥፩።
"ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።" መዝ ፹፫፥፯።
"ንጉሡም ዳንኤልን፦ ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው።" ዳን ፪፥፵፯።
፪. የጌቶች ጌታ
"ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል።" እንዲል ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ፩ጢሞ ፮፥፲፭። እንዲሁም ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) ቅዱስ ዮሐንስ "በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።" ሲል እንደተናገረ፡፡ ራእይ ፲፯፥፲፬።
ሊቀ ነቢያት ሙሴም "እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ" እንዲል፡፡ ዘዳ ፲፥፲፮።
ከዚህም በላይ የነገሥታት ንጉሥ የሚለውም መጠሪያ ለባሕርዪ ንጉሥነቱ ይቀጸልለታል፡፡ ይህንን የእግዚአብሔርነቱ መለያ እና መጠሪያ በሌላ መልኩ እናቆላምጣለን እያልን መስመር የለቀቀ አጠራር እንዳናበጅ መጠንቀቅ ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ እነዚህን ሁሉ ይጨምራልና፡፡ ለመሆኑ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ብሎ መጥራት ችግር አለውን? የሚለው ጥያቄ በአእምሯችን እየተጉላላ እንደሚገኝ አስባለሁ፡፡
አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ብሎ መጥራት ችግር አለውን?
እግዚእ ማለት ጌታ ሲሆን አጋእዝት ማለት ደግሞ ጌቶች ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሚል የዓለም ጌቶች ሥላሴ እያለ ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በመለኮቱ አንድ በመሆኑ አምላኮች እንደማንል ሁሉ ጌቶችም እንል ዘንድ አይገባም፡፡ በጌትነቱ እግዚአብሔር አንድ ነውና ጌቶች ብሎ መጥራት ጸያፍ ይሆንብናል፡፡ ስለሆነም በተለምዶ አጋእዝተ ዓለም እያሉ መጥራት መቆም ይኖርበታል፡፡ "እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው" ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ማር ፲፪፥፳፱። ደግሞም "አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት" ብሎ ቅዱሱ ሐዋርያ እንደተናገረ፡፡ ኤፌ ፬፥፭።
አንዳንድ ጊዜ በልማድ የሚነገሩ አባባሎች ከመቆየታቸው እና በጊዜ ባለመታረማቸው የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ቅቡልነት እንዳላቸው ተደርገው በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም አንዱ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ የሚለው አጠራር ይገኝበታል፡፡
በቅዳሴ ማርያም ላይ "አንቺን የወደደ እግዚአብሔር አብ ቅዱስ ነው፣ በማኅፀንሽ ያደረ ወልድ ዋሕድም ቅዱስ ነው፣ ያጸናሽ የጽድቅ መንፈስ ጰራቅሊጦስም ቅዱስ ነው፡፡" ይላል፡፡ እንዲህ እንበል እንጂ ቅድስት ሥላሴ ከምንል በስተቀር አብዝተን ቅዱሳን ሥላሴ አንልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ የሚለውን ቅጽል ለሦስቱም ስሞች ለየብቻ ሲጠራ ይጠቀም እንጂ ሦስቱ ቅዱስ ተደምሮ ቅዱሳን ወደሚል አይመጣም፡፡ ቅድስና የሦስቱም አካለት አንድ ባሕርዪ ነውና፡፡ ይህ ማለት በተለምዶ አንዳንድ ሰዎች ሦስቱ ሥላሴ እንደማለት ይሆናል፡፡ ሦስቱ ሥላሴ ማለት ሦስት ሥላሴዎች አሉ እንደማለት ነው፡፡ እኛ የምናውቀው አንድ ሥላሴ እንጂ ሦስት ሥላሴ አይደለም፡፡ ሦስቱ ሥላሴ አልን ማለት ዘጠኝ መለኮት ወደሚለው ስሁት ትምህርት ይወስዳል፡፡
እንደ አሳት የሚፋጀውን ዙፋኑን የሚሸከሙት ጸወርተ መንበር ኪሩብ ምስጋና ሲያቀርቡ "ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች" እያሉ ሲሆን ሦስት ጊዜ ቅዱስ የሚለውን ቃል ለአንዱ እግዚአብሔር እንደሰጡት ስናይ አንዱ ቅዱስ አብ፣ አንዱ ቅዱስ ደግሞ ወልድ፣ አንዱ ቅዱስም መንፈስቅዱስ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ኢሳ ፮፥፫። ሦስት ጊዜ ቅዱስ ካሉ በኋላ "ከክብሩ" የሚለውን ሲናገሩ አንድ መሆኑን ነግረውናል፡፤ ከክብሩ በማለት ፋንታ ከክብራቸው ብለው ቢሆን አብዝተው ተናገሩ ባልን ነበር፣ ነገር ግን ምሥጢር ጠንቅቀው ተናግረዋልና እነርሱን አብነት ልናደርግ ይገባል፡፡
በዮሐንስ ራእይ የተባለውም ይኽንኑ የበለጠ ጉልህ ያደርግልናል፡፡ "አራቱም እንስሶች...ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም።" ሲል ሦስት ጊዜ ቅዱስ እያሉ ከጠሩ በኋላ "የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ" ሲል አንድ አድርጎ ነው፡፡ ራእይ ፬፥፰። ሦስት ጊዜ ቅዱስ ማለታቸው በስም፣ በአካል፣ በግብር ሦስትነት ያለውን እግዚአብሔርን መጥራት ሲሆን መለኮታዊ ሥልጣኑን ሲጠቅሱ ግን በአንድነቱ መጥራታቸው እግዚአብሔር በመለኮቱ፣ በሥልጣኑ፣ በጌትነቱ አንድ ነው ሲሉን ነው፡፡
ሠለሰ የሚለው ቃል በቁሙ ሦስት አደረገ ማለት ነው፡፡ ሥላሴ ማለትም ሦስት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሥላሴ የሚለው ቃል ራሱ ብዙነትን የሚያሳይ ስለሆነ በእርሱ ላይ ሌላ የሚያበዛ ቅጽል ሁለቱ ወይንም ሦስቱ እያልን የምንቀጥል ከሆነ በቅጽሉ ቁጥር ልክ እያበዛነው እንሄዳለን ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ሥላሴ ብንል ሁለት የተለያዩ ሥላሴ አሉ ማለት ይሆንብናል፡፡ እንደዚሁም ሦስቱ ባልን ጊዜ እንደዚያው የሦስትን ብዜት ይዞ ይቀጥልና ከመሠረታዊው ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳናውቀው ማፈንገጥ ይመጣል፡፡ ሳናውቅ ተሳስተን ሌላ ሰውንም እናሳስታለን፡፡
ስለሆነም እግዚአ ዓለም ሥላሴ ልንል እንጂ አጋእዝተ ዓለም ልንል አይገባም፡፡ ቅድስት ሥላሴ እንላለን እንጂ ሦስቱ ሥላሴ አይባልም፡፡ ቅድስት ብለን በሴት አንቀጽ መጥራታችንም ጾታ ለመስጠት ሳይሆን የሥላሴ ቸርነት እና ርኅራኄ ልክ እንደ እናት ስለሆነ ያንን ለማዝከር ሲባል ቅድስት እንላለን፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እግዚአብሔር አባታችን ነውና ሥሉስ ቅዱስ ብለንም እንጠራዋለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ሥላሴዎች ብሎ መጥራትም የማይገባ አነጋገር እንደሆነ ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ ሥላሴዎች ካልን ብዙውን መልሰን አበዛነው ማለት ሲሆን ከአንድ በላይ ሥላሴ የጠራን ያስመስላል፡፡ ከአንድ በላይ ሥላሴ የለምና የሌሉትን ብንጠራ ምን እንጠቀማለን፡፡ አያውቁም ተብለን ከመተቸት በቀር ሌላ ምን እናተርፋለን፡፡
ከበዓሉ ረድኤቱን በረከቱን ያሳድርብን!
(መ/ር አባይነህ ካሴ)

Пікірлер: 4

  • @user-ob4tn4vz5r
    @user-ob4tn4vz5rАй бұрын

    ኣሜን ኣሜን ኣሜን

  • @user-wl8iz4tc1p
    @user-wl8iz4tc1pАй бұрын

    💒አሜን አሜን አሜን🙏🙏🙏🎉🎉🎉

  • @AsefuMeseleui9no
    @AsefuMeseleui9noАй бұрын

    Amen Amen Amen ❤❤❤

  • @Habeeba-oz7rp
    @Habeeba-oz7rpАй бұрын

    ❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤ellllllelllllll·lll elllllllllllll·lllll

Келесі